የአይሲል (ISIL) እንቅስቃሴ ምንነትና አንደምታው (ከአንድ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ ዕይታ)

የአይሲል (Islamic State of
Iraq and the Levant – ISIL)
እንቅስቃሴ ከሰማይ ዱብ ያለ አዲስ
ክስተት አይደለም። አይሲል
( አንዳንዶቹ ISIS ይሉታል –
Islamic State of Iraq and
Syria ) በመካከለኛው ምሥራቅ
ያለው የፖለቲካ ውጥንቅጥ ሀቅ
ውጤት ነው። ለአነሳሱ፣ ለዕድገቱና
ለሂደቱ ብዙ ነባሪ ምክንያቶች
አሉት። በርግጥ የአይሲልን
እንቅስቃሴ ከሀይማኖትና ከዘይት
ሀብት ለይቶ ማየት አይቻልም።
በፍልጥዔማውያንና
በእስራዔላውያን መካከል ያለው
ማብቂያ የለሽ ያልተቋረጠ ጦርነት
አንዱ ምክንያቱ ነው። በኋላ ቀር
የአረብ ነገሥታትና በሥራቸው
የሚሰቃየው ሕዝብ የኑሮና የሀብት
ሥምሪት መራራቅ ሌላው
ምክንያቱ ነው። በእስልምና
አጥባቂዎችና ለዘብተኛ ተከታዮች
መካከል ያለው የግንዛቤ ልዩነት
ሌላው ምክንያቱ ነው።
አሜሪካኖች የራሳቸውን ጥቅም
ለማስጠበቅ በቦታው የሚፈጥሩት
ጣልቃ ገብ ፈትፋችነታቸው
ቀንደኛው ምክንያቱ ነው።
የሩስያኖች በቦታው ከአሜሪካኖች
ጋር በመወዳደር የሚያደርጉት
ጣልቃ ገብነት ሌላው ቀንደኛ
ምክንያቱ ነው። የእስራዔል
በቦታው በየመኖርና ባለመኖር
መካከል ያላት የግብግብ ስሌት
ሌላው ምክንያቱ ነው።
የፍልስጥዔማውያንን የነፃነት ትግል
በመደገፍና ባለመደገፍ
በመካከለኛው ምሥራቅ
መንግሥታት ያለው ሥምሪት ሌላው
ምክንያቱ ነው። በተጨማሪ
በሺዓይትና ሱኒ መካከል ያለው
የሃይማኖቱንና የትግባር
አተረጓጎም ልዩነትና የተከታዮቻቸው
ውድድር ሌላው ምክንያቱ ነው።
ኢራን፣ ሳውዲ ዓረቢያ፣ ሶሪያ፣
ቱርክ፣ የሚጫወቱት ሚና ሌላው
ምክንያቱ ነው። ዘይት የመዘመዘው
የሀብት ክምችትና በሰዎች መካከል
ያስከተለው መለያየት ሌላው ቀንደኛ
ምክንያቱ ነው። ባጭሩ የአይሲል
እንቅስቃሴ የተመሰቃቀለ ነው።
ዛሬ አሜሪካኖች ያለ የሌለ
የቴክኖሎጂ ግኘቶቻቸውን
አዋቅረው፤ ከአረብ ነገሥታት
የሚያገኙትን የዘይት ገንዘብ
ስብስበው፤ ሟች ወጣቶችን
አንጋግተው አይሲልን ቢወግሩት፤
ነገ በሌላ መልኩ የሚቀጥል
እንቅስቃሴ በመካከለኛው
ምሥራቅ ይፈለፈላል። በዚህ
ጽሑፍ፤ በዚህ ዙሪያ
በኢትዮጵያዊነቴ፤ በኔስ በኩል ምን
አለ? በማለት ያዋቀርኩትን
ኢትዮጵያዊ ግንዛቤ ላካፍላችሁ።
እንግሊዞች በመካከለኛው ምሥራቅ
ዘልቀው ቦታውን ማመስ ከጀመሩ
ወዲህ፤ ከአካባቢው ሰላም ርቋል።
ይኼንኑ ነውና የፈለጉት፤ ከዚያ ጊዜ
ወዲህም ሳያርፉ፤ አካባቢውን
ሲያምሱ መኖራቸው ለሁላችንም
ግልጽ ነው። ቅኝ ገዥዎች ዋናው
ዓላማቸው፤ በወቅቱ ያለውን ያካባቢ
ንብረት ከመዝረፍ ሌላ፤ ለቀው
ሲወጡ፤ በዚያ አካባቢ ሰላም
እንዳይኖር፤ እንቅፋት ተክለው
መውጣት ነው። ይህን እንግሊዞች፤
በሕንድና በፓኪስታን፤ በራሳችን
ሀገር በኤርትራና በቀሪው
የኢትዮጵያ ክፍል፤ በያንዳንዱ
በገዙት ሀገር ሁሉ የኖረ መታወቂያ
ቅርሳቸው ነው። አርበኞቻችን
ጎንደርን ሊይዙ ከመተማ ተነስተው
በሰቀልት ብቅ ሲሉ፤ ከጣሊያን
ፋሽስቶች ጋር በመመሣጠር፤
ንብረታቸውን ሁሉ ተረክበው፤
አርበኞች ጎንደር እንዳይገቡና
ፋሽስቶችን እንዳይወጉ እናም
ንብረቱን እንዳይወስዱ ተከላክለው፤
በገዛ ሀገራችን፤ አርበኞቻችንን
ከልክለዋቸዋል። በርግጥ በጥቁር
ላይ ያላቸው ጥላቻና ንቀት፤
በኢትዮጵያዊያን አርበኞች ላይ
ያላቸው ቂም ተደምሮ፤ በየትም
ቦታ የሚያደርጉትን መረዳቱ ቀላል
ነው። ይህ ፈረንሳዮችም ሆኑ
ጣሊያኖች፤ ቤልጂጎቹም ሆኑ
ስፓኒያርዶች፤ ሁሉም የተከተሉት
የቅኝ ግዛት መመሪያቸው ነው።
በተለይ የጎሳ ክፍፍል ጨዋታቸው፤
በነጭ አውሮፓዉያን መካከል ዋና
ነቀርሳ መሣሪያቸው ነው።
በአፍሪቃ ውስጥ አሁን ያሉትን
ብጥብጦች መሠረት ብንፈልግ፤
ዋናው ምንጩ ቅኝ ገዥዎች
ሆነው፤ ሌላው ቀሪው፤ እኒሁ ቅኝ
ገዥዎች ያሠለጠኗቸው ሀገር በቀል
የፖለቲካ ሊሂቃን ሆነው እናገኛለን።
ይህ የነቀርሳ ውርስ አሁንም በኒሁ
ቅኝ ገዥዎች ባሰለጠኗቸው ሀገር
በቀል አደግዳጊዎች እያመረቀዘ፤
ሰላም በየአካባቢው እንዳይኖር
አድርጓል። በርግጥ ከላይ
እንዳስቀመጥኩት የአይሲልን
እንቅስቃሴ ከሀይማኖትና ከዘይት
ሀብት ለይቶ ማየት አይቻልም።
እነዚህን የዘይት ሀብትና
የሃይማኖት ጨዋታዎች ደግሞ
ከእንግሊዝ፣ ከአሜሪካንና ከሩስያ
ገንጥሎ ማስቀመጥ አይቻልም።
በፍልጥዔማውያንና
በእስራዔላውያን
መካከል
ያለው
ማብቂያ
የለሽ
ያልተቋረጠ
ጦርነት
አንዱ
ምክንያት
ነው
ብያለሁ።
በእስራኤሎችና
በፍልስጥዔማዉያን መካከል ያለው
ጠብ እንዳለ ሆኖ፤ ራሱን የቻለና
በጣም የተመሰቃቀለ ጉዳይ ነውና
ለሌላ ጊዜ ትተን፤ ይህ ጉዳይ አሁን
እየተካሄደ ላለው የአይሲል
እንቅስቃሴ ምን ዓይነት አስተዋፅዖ
አድርጓል? የሚለውን እንመልከት።
በፍልስጥዔማውያንና
በእስራኤላዊያን መካከል ለዘመናት
የኖረ ጠብ አለ። የዚህን ምንጭ
ብዙ ሳይሄዱ መረዳት ይቻላል።
ሆኖም ለያዝነው ርዕስ ትኩረት
በመሥጠት፤ በሃያ አንደኛው ክፍል
ዘመን ለዚህ ጉዳይ መፍትሔ
መሥጠት አለመቻሉ በጣም
ያስገርማል። ይህ በመካከለኛው
ምሥራቅ ጎልቶ የሚታየው ጠብ፤
በአንድ በኩል እስራኤሎችን በሌላ
በኩል ደግሞ ፍልስጥዔማውያንን
አሰልፏል። በፍልስጥዔማውያን
መካከል ለዘብተኞችና አክራሪዎች
አሉ። በነኚህ የፍልስጥዔማውያን
መካከል የሚዋልል ግንኙነት አለ።
አንደኛው ክፍል ከእስራኤል ጋር
አብሮ ለመኖር ሲዳዳ፤ ሌላው ክፍል
ደግሞ መሬታችን የፍልሥጥዔሞች
መሬት ነው። ቅኝ ገዥዎች
ያመጡብን ጣጣ ነው ይላል።
እስራዔሎች ደግሞ ታሪካዊ
ባለቤትነት አለን ባዮች ናቸው። ይህ
በመካከላቸው ያለው ጠብ፤
ደጋፊዎችን በማሰለፍ በኩል፤
የአረብ ሀገሮችንና ምዕራባዊያንን
ለያይቶ አስቀምጧል። እኔም
አለሁበት ባይ ሩስያም በበኩሏ
ጣቷን አስገብታለች። ይህ ጠብ
የዘይቱን ፍላጋ ካለው ፖለቲካ
ተጨምሮ፤ ቋሚ ሆኗል። በዚህ
የአይሲል እንቅስቃሴ የተኮለኮሉት፤
እስራዔልን ማጥፋት አንዱ
መርኋቸው ነው። ስለዚህ
የእስራዔሎችና የፍልስጥዔማውያን
ጦርነት፤ ለአይሲል እንቅስቃሴ
ቀጥተኛ አስተዋፅዖ አለው።
በኋላ ቀር የአረብ ነገሥታትና
በሥራቸው የሚሰቃየው ሕዝብ
የኑሮና የሀብት ሥምሪት መራራቅ
ሌላው ነው። ቀደም ሲል የአረብ
መንግሥታት መሪዎች ከሃይማኖት
ጋር በጣም የተጣበቀ ትስስር
ነበራቸው። በአካባቢው ዘለዓለማዊ
የበላይነት እንዲኖራቸው የሰለቱት
ቅኝ ገዥዎች፤ የሚከተላቸውን
መንግሥታዊና ወታደራዊ
መዋቅሩን ካስተካከሉ በኋላ ጥለው
ሲወጡ፤ ጊዜውና የዓለም ጉዞ ሂደት
ሆኖባቸው፤ ለውጥ ማስከተል ግድ
ሆነ። ነገር ግን፤ በቦታው
የተቀመጡት ነገሥታቶችና
አምባገነኖች፤ ከቅኝ ገዥዎቻቸው
እንደተማሩት ሁሉ፤ ከሥራቸው
ያለውን ሕዝብ እንደባሪያ መግዛት
ቀጠሉበት። ድንገት ብቅ ያለው
የዘይት ሀብት፤ ከላይ እስከታች
ያለውን ጉዳይ በጠበጠው። በነኚህ
ገዥዎች እቅፍ የተዘረገፈው
ንብረት፤ ያሻቸውን ለማድረግ በር
ከፈተላቸው። የኛን ሀገር የፖለቲካ
ምኅዳር ከመበጥበጥ ጀምሮ፤
በራሳቸው ሕዝብ ላይም
የሚያደርጉትን ቅጥ ያጣ ድፍረት
መለኪያ አሳጣው። በዚህ ላይ
ምዕራባዊያኑ ከጀርባ ሆነው
የጥቅሙ ተካፋይና የወስኝነትም
ሚናቸውን አስፋፉ። እናም
ለሃይማኖቱ ተቆርቋሪ የሆኑትና፤
በተለይም የውጪ ዜጎችን በቦታው
መንቀሳቀስ ያልወደዱት አረቦች፤
ከነዚህ ውስጥ በየቤተ መንግሥቱ
ካሉት ግለሰቦችም ጭምር፤
አኮረፉ። እናም ውስጥ ውስጡን
የዚህ እንቅስቃሴ የውስጥ አርበኞች
ሆኑ። ስለዚህ የገዥዎቹ ተግባር
ለዚህ እንቅስቃሴ አስተዋፅዖ
አድርጓል።
የመካከለኛው ምሥራቅ፤ አሁን
በዓለም ዙሪያ ካሉት ዋና ዋና
ሃይማኖቶች የሶስቱ ምንጭ ነው፤
ለክርስቲያኖች፣ ለሙስሊሞችና
ለቤተ እስራኤሎች። በርግጥ
ቀደም ብሎ የነበረው ጥንታዊው
የዞራስተር ሃይማኖትም ምንጩ
ይኼው አካባቢ ነው። የሃይማኖት
ጉዳይ በኑሮ ደረጃ፤ በተለይም
በአስተዳደር ዙርያ ሲገባ፤ የሥጋና
የነፍስን ወሰን ያፈርሰዋል።
ሥጋንም እንደነፍስ መመዘን
ይፈልጋል። ይህ ደግሞ በግለሰብ
ደረጃ የሃይማኖቱ ተከታይ ከመሆን
አልፎ፤ አንድ ለአንድ በአምላኩና
በግለሰቡ መካከል ያለው ግንኙነት
ተቀይሮ፤ በስብስብና በአምላካቸው
እንዲሆን ግዴታ ያደርጋል። ይህ
መሠረታዊ የሆነው ጉድለት፤
ሃይማኖቱን በመተርጎም ላይ
ከፍተኛ ጫና እያስከተለ፤ ለጦርነት
በር ይከፍታል። ለአንድ ሺ ዓመታት
አንድ የነበረችው የክርስትና
ቤተክርስቲያን፤ ለሁለት ተከፈለች።
ለሁለት በተከፈለው የክርስትና ቡድን
አባልነቱ፤ የግለሰብ ፍላጎት ሳይሆን፤
የገዥዎቹ ፍላጎት ሆነ።
በምሥራቃዊው የክርስትና
ተከታዮች (ኮንስታንቲኖፕል
ማዕከሉ) እና በምዕራባዊው
የካቶሊክ ቤተክርስትያን (ሮም
ማዕከሉ) የነበረው ክፍፍል ይኼው
ነው። ከዚያ በሮምና በጀርመኖቹ፤
ከዚያም በስዊትዘርላንድ
በእንግሊዝ እያለ ክፍፍሉ ቀጠለ።
በእስልምናም ዘንድ ይሄ የምናየው
የሽዓይት፣ የአላዋይትና የሱኒ
ክፍፍል እንዲያው ነው። መቸም
ጥቅልል ባለ መልኩ እንዲህ
ሲቀርብ ብዙ የሚጎድል እንዳለ
እየተቀበልኩ፤ ለጽሑፉ ሂደት
ይረዳኝ ዘንድ ግን ጥቅሉን
መቀበሉ ግዴታዬ ሆኗል። እናም
ገዥዎች የሃይማኖትም የበላይነት
በመላበሳቸው፤ ለአይሲል መፈጠር
ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርገዋል።
በእስልምና አጥባቂዎችና ለዘብተኛ
ተከታዮች መካከል ያለው የግንዛቤ
ልዩነት ሌላው ነው። መቸም
የሃይማኖት ጉዳይ ችግር
የሚያስከትለው፤ “እኔ የበለጠ
ሃይማኖተኛ ነኝ። የኔው ነው
ትክክል እንጂ ያንተው ትክክል
አይደለም።” የሚለው ነው። ይህ
ነጥብ ደግሞ አይቀሬ ነው።
ምክንያቱም፤ ሌላም ትክክል አለ
የሚል ጥርጣሬ ያለው ግለሰብ
አማኝ፤ የራሱን ብቸኛ ትክክል ነው
ብሎ እንዳይቀበል ስለሚያግደው፤
ሌሎች በሙሉ ስህተተኞች ናቸው
የሚለውን ማስመር አለበት።
አንደኛው የክርስትና ዘርፍ
ሌላኛውን የክርስትና ዘርፍ
ማጣጣሉ ከዚህ የመጣ ነው።
በእውነት ታሪክና የሃይማኖታቸው
ምንጭ አንድ ሆኖ፤ በሂደት ሊለያዩ
ያበቃቸው፤ ሃይማኖቱ ስላደገ
ወይንም ስለጠወለገ ሳይሆን፤
የነፍስን ጉዳይ ከሥጋ በማዛመድ፤
እኔ የምልህን ስማ የሚል ቀጭን
ትዕዛዝ ሰጪ ስለመጣ ነው። ይህ
ደግሞ በግልፅ የሥጋ ክልል እንጂ
የነፍስ ክልል አይደለም። ታዲያ
አጥባቂና ለዘብተኛ የሚባሉት፤
ከሥጋ ፍላጎት አንጻር እንጂ፤ የነፍስ
ክልል ከሆነው መሠረት አይደለም።
በአንድ አምላክ እናምናለን
የሚሉና፤ ሁሉም ሰዎች
በአምላካቸው አምሳያ የተፈጠሩ
ናቸው ብለው የሚቀበሉ አማኞች፤
የአምላካቸውን ፍጡር እነሱ ዳኛ፣
እነሱ ፍርድ ሰጪ ሆነው፤ ይኼን
ካልተቀበልክ ብሎ መግደል
በፍፁም አይቀናቸውም ነበር።
ሆኖም ግን ይህ ለአይሲል መነሳትና
ማደግ አስተዋፅዖ አድርጓል።
አሜሪካኖች የራሳቸውን ጥቅም
ለማስጠበቅ በቦታው የሚፈጥሩት
ጣልቃ ገብ ፈትፋችነታቸው
ቀንደኛው ምክንያቱ ነው። አሜሪካ
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ላይ
የበላይ ሆናና የኮሚኒስትን
መስፋፋት አጋች ሆና በዓለም ዙሪያ
ክንፏን ከዘረጋች ጀምሮ፤ የራሷን
ጥቅም ለማስጠበቅ፤ ዛሬ ቻይና ለኔ
እስከጠቀመኝ ድረስ ብላ አምባገነን
መሪዎችን በዓለም ዙሪያ
እንደምታሽሞነሙን ሁሉ፤ እርሷም
የአምባገነኖች አሽሞንሟኝ
ነበረች። አሁንም ነች። ቺሌ ውስጥ
አዬንዴን አስገድላ የፒኖቼን
አምባገነን መንግሥት መትከሏ በቂ
ማስረጃ ነው። ዛሬም ለወራሪው
የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር
መንግሥት የምታደርገው ድጋፍ ለኛ
ተጨማሪ ማስረጃ ነው። ወደ
አይሲል ስንመለስ፤ ቡሽና ቼኒ
የፈጠሩት የውሸት ጋጋታን ተከትሎ
የመጣው የኢራቅ ወረራ፤
ለመፈጠራቸው መሠረቱ ነው።
አስከትለውም “ዲ ባዚፊኬሽን”
ብለው ሱኒዎችን ከመንግሥት
ማንኛውም ተሳትፎ አባረሯቸው።
በርግጥ የኑሪ ማላኪ የሺዓይቶችን
የበላይነት ለማሳየት ሱኒዎችን
ድምጥማጣቸውን ከመንግሥት
መዋቅሩ ማጥፋቱ ተከትሎ የመጣ
ጉድ ነው። ይህ የአሜሪካኖች
ጣልቃ ገብነትና ያቋቋሙት
የማሊኪ መንግሥት፤ የሱኒ
ወታደራዊ መዋቅሩን ከሥር
መሠረቱ ድምጥማጡን አጥፍቶ
ጄኒራሎችን ቁሻሻ እንደነካ በትር
አውጥቶ መጣሉ፤ የአይሲል
መፈጠር አይቀሬ መሆኑን አወጀ።
እናም አሜሪካኖች ቀንደኛው
ምክንያት ናቸው።
የሩስያኖች በቦታው ከአሜሪካኖች
ጋር በመወዳደር የሚያደርጉት
ጣልቃ ገብነት ሌላው ቀንደኛ
ምክንያቱ ነው። በሩሲያ በአሜሪካ
የነበረው ጠብ እኔ እበልጣለሁ
የለም እኔ እበልጣለሁ ነበር።
ይኼውም በርዕዩተ ዓለም ተደግፎ፤
የሶሺያሊስት እና የካፒታሊስት ሠፈር
ተብሎ ተለይቶ፤ የቀዝቃዛው
ጦርነትን ዘመን አዋቅሮታል። ከዚያ
ወዲህ፤ መሠረታዊ የሆነውና በሥሩ
ተሰምሮ የኖረው የጥቅም
ስግብግብነቱ ጎልቶ ወጥቷል። ምን
ጊዜም ቢሆን እኔ ልጠቀም እኔ
ልጠቀም ነበር ሩጫው። አሁንም
የንዋይ ውድድሩ አይሏል። ሩስያ
አሜሪካ በሂደችበት እኔም አለሁ
ማለቷ አዲስ አይደለም። አሁንም
የሶሪያውን አሳድ በመደገፍና እንደ
ኢትዮጵያ በሶሪያ ውስጥ ላለው
የጥቂቶች ጠባብ ወገንተኛ
መንግሥት የምታደርገው አብሮ
መቆም፤ ለሀገሪቱ የሱኒ ተከታዮች
ለአይሲልን ድጋፍ እንዲሠጡ
መንገድ አበጀ። እናም በኢራን፣
በሶሪያና በቀድሞ የሶቪየት አካል
የነበሩ የደቡብ ጎረቤቶቿ ጣልቃ
ገብነት፤ ለአይሲል መፈጠርና ማደግ
አስተዋፅዖ አለው።
የእስራዔል በቦታው በየመኖርና
ባለመኖር መካከል ያላት የግብግብ
ስሌት ሌላው ምክንያቱ ነው።
እስራዔል የምትከተለው
የፍልስጥዔማውያንን መከፋፈልና
ርስ በርስ ማጣላት ስልት፤ ሰላም
በመካከለኛው ምሥራቅ እንዳይኖር
አንዱ ምክንያት ነው። ይህ
በመካከላቸው የተፈጠረው ክፍፍል
ደግሞ በራሱ፤ ሌሎች ችግሮችን
አስከተለ። ገሚሶቹን አክራሪ
ሲያደርጋቸው፤ አብዛኛውን ሕዝብ
ደግሞ ተስፋ እንዲቆርጥ
አደረገው። ይህ ሁኔታ ደግሞ፤
ለጥቃቅን ጉዳዮች ክብደትን
በመሥጠት ለሚያርገበግቡት ራስ
ፈጣር የችግር ደራሾች፤ የፈጣሪነት
ሚና ከፈተላቸው። እናም በሶሪያ፣
በሳዑዲ አረቢያ፣ በጆርዳን፣ በግብፅ፣
በሊባኖስ፣ በቱርካን በአብዛኛው
የእስልምና ተከታይ ሀገሮች፤
ለአክራሪዎች መፈልፈል ለም
መሬት አዘጋጀ። ስለዚህ እንኳን
በነዚህ ሀገሮች፤ በምዕራባዊያኖቹ
በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ፣
በፈረንሳይና በጀርመን ተከታዮችን
ማፍራት ቀላል ሆነላቸው። ይህ
ሌላው ምክንያት ነው።
የፍልስጥዔማውያንን የነፃነት ትግል
በመደገፍና ባለመደገፍ
በመካከለኛው ምሥራቅ
መንግሥታት ያለው ሥምሪት ሌላው
ምክንያቱ ነው። ሰላም በአካባቢው
እንዳይኖር የጣሩት ቅኝ ገዥዎች፤
ዛሬ ተቆርቋሪ በመምሰል የሰላም
አቀንቃኞች ነን ቢሉም፣
በመካከለኛው ምሥራቅ ላለው
ችግር ተጠያቂዎቹ እነሱ ናቸው።
የፍልስጥዔማውያን ችግር፤ ለረጂም
ዘመን ከመቆየቱ የተነሳ፤ የተከፋፈለ
ምኞትና የትግል መንገድ
አብጅቷል። እናም በመካከላቸው
የማይታረቅ ቅራኔ ተፈጥሯል።
ይኼ ደግሞ አንድም ትግላቸው
እንዳይሳካ ሌላም ርስ በርሳቸው
እንዲጠፋፉ ምክንያት ሆኗል። ይሄ
በወጣቱ ተስፋ የማጣትና የሥር
ዕድል አለማግኘት ውጤት የሆነው
የኢንቲፋዳ ንቅናቄ፤ ውሎ አድሮ
ከፍ ያለ ችግር እንደሚፈጥር ግልፅ
ነበር። ይኼው የአይሲል ጉዳይ ከዚህ
ጋር የተጣበቀ ነው።
ተጨማሪ በሺዓይትና በሱኒ
መካከል ያለው የአተረጓጎም
ልዩነትና የተከታዮቻቸው ውድድር
ሌላው ምክንያቱ ነው። ይኼን ነጥብ
አስመልክቶ ከላይ ደርቤ
ስለተነተንኩት፤ መጣፊያ
አያስፈልገውም።
ኢራን፣ ሳውዲ ዓረቢያ፣ ሶሪያ፣
ቱርክ፣ የሚጫወቱት ሚና ሌላው
ምክንያቱ ነው። ኢራንና ሳዑዲ
አረቢያ የእስልምና ማዕከል እኔ ነኝ
የለም እኔ ነኝ የሚለው
ፉክክራቸው፤ የዋለ ያደረ ነው።
ሁለቱም የዘይት ክምችት
ስላሰከራቸው፤ በገንዘብና በጉልበት
የማዕከሉን ባለቤትነት ለመያዝ
የማያደጉት የለም። ሶሪያ የአንድ
ቤተሰብ አምባገነንነትና የጠባብ
ወገንተኛ አናሳ ክልል የበላይነት፤
በሶሪያ ሕዝብ ላይ የሚያደርሰው
በደል፤ ለዚህ ለአይሲል መነስታና
ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው።
ቱርክም በከርዶች ላይ
የምታደርሰው በደል ሲደመርበት፤
በጠቅላላ በአካባቢው ማንነትና
እምነት፤ ሀብትና ማጣት
ተቀላቅለውበት፤ አካባቢውን እግር
የሚለበልብ የጋለ መሬት
አድርገውታል። እንግዲህ በዚህ ላይ
ደግሞ ዘይት የመዘመዘው የሀብት
ክምችትና በሰዎች መካከል
ያስከተለው የኑሮ መለያየት፤
ለአይሲል ክስተት ቀንደኛ ምክንያቱ
ሆኗል። ባጭሩ የአይሲል
እንቅስቃሴ የተመሰቃቀለ ነው።
ለአንድ ኢትዮጵያዊ፤ የአይሲል
ሁኔታ ለምን አቅሉን ይስበዋል?
የሚለው ነው ዋናው ጉዳዬ።
በሀገራችን በኢትዮጵያ፤ እንደሌሎቹ
የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገሮች
ሁሉ፤ የማንነትና የእምነት ጉዳይ፤
የፖለቲካ አመለካከትን ጨፍግጎ
በመያዝ፤ ሰዎች በነፃ የአመለካከት
ግንዛቤያቸውን እንዳይዙ ሽምቅቆ
ይዟል። እናም የፖለቲካችን ሂደት፤
በማንነትና በእምነት ዙሪያ
እየተጠመጠመ፤ በእያንዳንዳችን
ኢትዮጵያዊያን ዘንድ፤ የግል ግንዛቤ
ከማሳደር ይልቅ፤ ትግሬ ስለሆንኩ፣
ኦሮሞ ስለሆንኩ፣ ሙስሊም
ስለሆንኩ የሚለውን እንድናጎለብት፤
ወራሪው የትግሬዎች ነፃ አውጪ
ግንባር የዕለት ተዕለት ትግባሩ
አድርጎታል። እኛም
ተመችተንለታል። ስለዚህ፤ የአይሲል
መረብ ጣዮች፤ አሜሪካን፣
እንግሊዝን፣ ፈረንሳይንና ጀርመንን
መመልመያ መስካቸው
እንዳደረጉት ሁሉ፤ ኢትዮጵያንም
ቦታቸው ለማድረግ አይጥሩም
ማለት ዘበት ነው። ምክንያቱም
የወራሪው የትግሬዎች ነፃ አውጪ
ግንባር መንግሥት ከአሜሪካ ጋር
ያለው ቁርኝት፣ በእስልምና
ተከታዮች ላይ የሚያደርሰው በደል፣
ለሶማሊያና ለሱዳን ያለው ቀረቤታ፣
ተደማምሮ አመቺነቱ ግልፅ ነው።
በስደት በአረብ ሀገሮች ያሉ
ኢትዮጵያዊያን የሚደርስባቸው
በደል ለዚህ የአይሲል ሰበካ
ያጋልጣቸዋል። አንድ ቁርጠኛ
እንቅፋት ሆኖ ያስቸገረው፤
ኢትዮጵያዊያን ሀገር ወዳድ
መሆናችን ነው። የክርስትያን ሆነ
የእስልምና ወይንም ሌላ እምነት
ተከታዮች፤ ለሀገራችን ያለን ፍቅር
ወሰን የለውም። እናም ሀገራችንን
የምንሸጥ ሆነን አልተገኘንም።
ይሄ ከሃዲዎችን አያጠቃልልም።
ስለዚህ በብዛት ያለነው በሀገር
የመጣ ቀልድ አናውቅም። ሆኖም
ግን፤ ስብልን የሚያጠፋ ጥቂት
አንክርዳድ ነውና ስጋቴ ከዚህ
ይመነጫል።
አሜሪካ በምንም መንገድ ይሄን
ክስተት በጉልበት ለታጠፋው
አትችልም። መፍትሔው ብዙ
ጅማት አለው። ብዙ አስሮ የያዛቸው
ጉዳዮች አሉ። እናም ቀላል
አይደለም። ላሁኑ ይሔን ካልኩ፤
በዚህ ሂሳብ እኔም አለሁ የምትሉ
ሃሳባችሁን አካፍሉንና እኔም
የናንተን ላዳምጥ።

Advertisements

About Weraba times

I am journalist Journalisten
This entry was posted in Uncategorized. Bookmark the permalink.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s